ኤች አይቪ ኤድስ ወደ ወረርሽኝ ደረጃ ለመድረስ የቀረው ትንሽ መሆኑን በመገንዘብ ችግሩን ለመከላከል ፈጣንና የተቀናጀ እንቅስቃሴ ሊደረግ እንደሚገባ ፕሬዝደንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ አሳሰቡ፡:
ፕሬዝደንቷ 14ኛው የሃገር አቀፍ የኤች አይቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ምክርቤት ጉባኤ መክፈቻ ስነ ስርዐት ላይ እንዳሉት የዛሬ ሰላሳ አመት ገደማ በሽታው መከሰቱን ተከትሎ ለተከታታይ አመታት በተወሰዱት እርምጃዎች መልካም ውጤቶች ተገኝተው ነበር፡፡ይህን በዘላቂነት የሚያስቀጥል ተከታታይ ስራ ባለመሰራቱና ትኩረቱ በመላላቱ ግን በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ የሀገራችን አካባቢዎች ወደ ወረርሽን ደረጃ ሊሸጋገር የቀረው ትንሽ ብቻ ነው ብለዋል፡፡
"ጊዜ ስለሌለን አሁኑኑ የጋራ ራዕይ መሰነቅ ፤ ችግሮቻችንን የለየና በቅድሚያ መሰራት ባለባቸው ተግባራት ላይ ያነጣጠረ መፍትሄ ለማምጣት መትጋት፤በጋራ መሰለፍ እና አሻግረን የምናየውን ድንቅ ውጤት ለማጣጣም እንነሳ፡፡በግልጽ ተወያይተን ሁሉንም አይነት ችግሮቻችንን ከስር መሰረቱ የሚፈታ ውሳኔ ላይ መድረስ ይኖርብናል፡፡ በተጨማሪም በዚህ አዳራሽ ቃል መግባት ብቻ ሣይሆን ተግባርም ወሳኝ ነውና ለሁለገብ እንቅስቃሴ ራሳችንን የምናዘጋጅ ቁርጠኞችመሆን ይጠበቅብናል፡፡"