Sunday, 16 June 2019 16:24

ፕሬዝደንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ በነገው ዕለት የሚከበረውን የአፍሪካ ህጻናት ቀንን በተመለከተ ያስተላለፉት መልዕክት Featured

  • Print
  • Email

ፕሬዝደንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ በነገው ዕለት የሚከበረውን የአፍሪካ ህጻናት ቀንን በተመለከተ ያስተላለፉት መልዕክት

ከ1983 ጀምሮ ሰኔ ዘጠኝ ቀን የአፍሪካ ህጻናት ቀን ተብሎ ይከበራል፡፡ዘንድሮም "ሰብዐዊነትና የላቀ ትኩረት ለህጻናት ደህንነት"በሚል መሪ ቃል ሀገራችንን ጨምሮ በመላው አፍሪካ ታስቦ ይውላል፡፡
ቀኑ እ.አ.አ በ1976 የደቡብ አፍሪካዋ ስዌቶ ከተማ ተማሪዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ እና ደካማ የሆነው የትምህርት ጥራት እንዲስተካከል ለመጠየቅ አደባባይ በመውጣታቸው የያኔው አፓርታይድ ሥርዐት ፖሊሶች እንደ ስመ ጥሩ ሄክተር ፒተርሰን ባሉ ህጻናት ላይ በወሰዱት እርምጃ የደረሰባቸውን ጭፍጨፋ ለመዘከር ያለመ ነው፡፡ በተጨማሪም አፍሪካውያን ህጻናት ጥራቱ የተረጋገጠ ትምህርት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ግንዛቤ ለመፍጠርም ሲባል ታስቦ የሚውል ቀን ነው፡፡
የህጻንነት እድሜ የሁሉም ነገር መጀመሪያ ነው፡፡ ህጻናትን በማነጽ የሚሰራ ተግባር ሁሉ ነገን ይወስናል፡፡ ነገ በእርግጥም ከዛሬ የተሻለ የሚሆነው በዛሬዎቹ ህጻናትና ልጆች ፤በነገዎቹ አገርንና ህዝብን በሚመሩ ትውልዶች ላይ በሚሰራው ስኬታማ ተግባር ነው፡፡ ህጻናትን ታሳቢ ያላደረገ የነገ ህልምና ውጥን ውጤታማነቱ እምብዛም ነው፡፡
በኢትዮጵያ የሕጻናትን መብትና ደህንነት ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው፡፡ ሆኖም ገና ብዙ ይቀረናል፡፡ የህጻናት ጤና፤ ትምህርት ፤ሥነምግባር እና ደህንነት ጉዳይ የሁላችንም ስለሆነ እያንዳንዱ ዜጋ፤ ቤተሰብ እና መላው ማህበረሰብ ሃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል፡፡ በችግር ላይ የወደቁ ህጻናትን ተቀናጅተን የሚቻለንን በማድረግ ወደ ተሻለ ህይወት እናሸጋግራቸው፡፡በዐሉን ስናከብርም እያንዳንዳችን በአጠገባችን ስላሉ ህጻናት እናስብ፡፡ከዚያ መልካሙን በማድረግ እና በማሳየት ተስፋ እንሁናቸው፡፡ በዚህ ረገድ የመንግስት ተቋማት ከወር ደመወዛቸው አንድ በመቶ በመቀነስ ለችግር ተጋላጭ ለሆኑ ህጻናት ለሚያደርጉት ወገናዊና ሰብዓዊ ድጋፍ እጅግ አመሰግናለሁ፡፡ ሌሎቻችንም ይህን መልካም ተግባር በመከተል የድርሻችንን እንወጣ፡፡
በመጨረሻም መልካም በዐል እንዲሆን እመኛለሁ ፡፡

Leave a comment