የኢፌዴሪ ፕሬዝደንት ክቡር ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ዊርቱ ግለ ታሪክ

 

የኢፌዴሪ ፕሬዝደንት ክቡር ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ዊርቱ ግለ ታሪክ

 

     ክቡር ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ዊርቱ መስከረም 27 ቀን 2006 .ም በተካሄደው የህዝብ ተወካዮች የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ላይ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዝደንት ሆነው ተመረጡ፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዝደንት ሆነው ከመመረጣቸው በፊት በቱርክ ሪፐብሊክ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሆነው አገልግለዋል፡፡

ክቡር ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ዊርቱ ከቱርክ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደርነታቸው ጎን ለጎን በጆርጂያ፣ በአዘርቤጃን፣ በካዛኪስታን እና በታጃኪስታን የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ተጠሪ አምባሳደር ሆነው ከመጋቢት 1998 እስከ መስከረም 2006 ድረስ ሰርተዋል፡፡

በቱርክ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ከመሾማቸው በፊት ከጥቅምት 1995 እስከ ጥቅምት 1998 ድረስ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የፌዴሬሽን ምክርቤት አፈ-ጉባኤ ሆነው አገልግለዋል፡፡

ክቡር ደ/ር ሙላቱ ተሾመ የፌዴሬሽን ምክርቤት አፈ-ጉባኤ ሆነው የተመረጡት መስከረም 30 ቀን 1995 .ም ሲሆን በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ታሪክ ውስጥ የምክርቤቱ ሁለተኛው አፈ-ጉባኤ ናቸው፡፡

ክቡር ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ሙሉ የስራ ጊዜያቸውን የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብን በማገልገል አሳልፈዋል፡፡የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ሆነው ከመመረጣቸው በፊት የግብርና ሚኒስትር ሆነው ከ1994-1995 ሃገራቸውን ያገለገሉ ሲሆን በዚህ አንድ አመት ጊዜም ውስጥ በጁሀንስበርግ ደቡብ አፍሪካ በተካሄደው የዓለም ቀጣይነት ያለው እድገት ጉባኤ፤የአለም አቀፉ የግብርና ልማት ፈንድ ምክርቤት 25ኛ ጉባዔ ፤ በ22ኛው የአለም የምግብና እርሻ ድርጅት የአፍሪካ ጉባዔ ላይ እንዲሁም በዓለም የምግብ ጉባኤ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን መሪ እና ተለዋጭ መሪ በመሆን ያገለገሉ ናቸው፡፡

ክቡር ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ የግብርና ሚኒስትር ሆነው ከመመደባቸው በፊት ከ1988-1994 የኢኮኖሚ ልማትና ትብብር ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር በመሆን አገልግለዋል፡፡

1988.ም የኢኮኖሚ ልማትና ትብብር ሚኒስቴር ስራ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ በዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ትብብር ውስጥ ከለጋሾች ጋር በሚካሄዱ የሁለትዮሽና የመልቲላትራል ድርድሮችና አመታዊ የምክክር መድረኮች የሚሳተፉ የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድኖችን በመምራት ሃፊነታቸውን ተወጥተዋል፡፡ በወቅቱ በኮሜሳ የሚኒስትሮች ምክርቤት ተሳታፊ የነበረውን የኢትዮጵያን ልዑካን ቡድን የሚመራው በክቡር ዶክተር ሙላቱ ነበር፡፡በተለይም በሰኔ 1990 በኬኒያ ፣ በሰኔ 1991 ሞሪሸስ እና በሰኔ 1992 ደግሞ በግብፅ ውስጥ የተካሄዱት ጉባዔዎች ላይ እንዲሳተፍ የተወከለው የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን መርተዋል፡፡ ከዚህም ሌላ የቶኪዮ አለም አቀፍ ጉባዔ ለአፍሪካ ልማት ሁለተኛው ስብሰባ መሪ በመሆን የሰሩ ሲሆን የኢትዮጵያን ልዑካን ቡድን ከመምራት በተጨማሪ ቶክዮ ላይ በህዳር 1989፣ ዳካር በመጋቢት 1990፣ ሀራሬ በሰኔ 1990፣ አዲስአበባ በመስከረም 1991 እና በመጨረሻም በቶክዮ ከጥቅምት 9-11/ 1991 የተካሄዱት ጉባዔዎች ራፖርተር በመሆን ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡

ክቡር ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ኢኮኖሚ ልማትና ትብብር ሚኒስቴርን ከመቀላቀላቸው በፊት በተለያዩ ሃገራት ተመድበው በአምባሳደርነት አገልግለዋል፡፡ከ1987-1988 ድረስ በቻይና ሪፐብሊክ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ፣ ከ1985-1987 በጃፓን የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር እንዲሁም በታይላንድ፣ ቬትናም፣ ኢንዶኔዢያ፣ አውስትራሊያ እና ፊሊፒንስ የኢትዮጵያ ተጠሪ አምባሳደር ሆነው አገልግለዋል፡፡ ክቡር ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ሙያዊ አገልግሎታቸውን የጀመሩት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ካውንስለር ሆነው ማገልገል ከጀመሩበት ከጥቅምት 1984 .ም አንስቶ ነው፡፡

የክቡር ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ሙያዊ ልምድ ጥናትና ምርምር ማድረግ እንዲሁም ማስተማርን ያካትታል፡፡ ከ1980-1982 በተፍትስ ዩኒቨርሲቲ የፍሌቸር የህግና የዲፕሎማሲ ትምህርት ቤት ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በሚሰሩበት ጊዜ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ተመራማሪና ረዳት ሌክቸረር ሆነው አገልግለዋል፡፡ ከዚህም ሌላ ከ1975-1977 ድረስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የደብረዘይት የእርሻ ኮሌጅና እንስሳት ህክምና ተቋም ረዳት ሌክቸረር ሆነው አገልግለዋል፡፡

በወለጋ ኢትዮጵያ በ1949 .ም የተወለዱት ክቡር ፕሬዝደንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ኦሮምኛ፣ አማርኛ፣ እንግሊዝኛ እና ቻይንኛ አቀላጥፈው የሚናገሩ ሲሆን ፈረንሳይኛም በመጠኑ ይሞክራሉ፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በ1975 .ም ከቤጂንግ ዩኒቨርሲቲ በፖለቲካል ኢኮኖሚና ፍልስፍና ዘርፍ አግኝተዋል፡፡በ1980 .ም ሁለተኛ ድግሪያቸውን በዓለም አቀፍ ህግ እንዲሁም በ1984 .ም ደግሞ በተመሳሳይ ዩኒቨርሲቲ በዶክትሬት ዲግሪ ተመርቀዋል፡፡የዶክትሬት ዲግሪ ኮርሶቻቸውን በቤጂንግ ዩኒቨርሲቲ እንዳጠናቀቁ በዓለምአቀፍ ግንኙነት ተጨማሪ ኮርሶችን ለመውሰድ ወደ ዩኤስ አሜሪካ ሄደው ነበር፡፡ክቡር ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ በሀርቫርድና ቱፈትስ ዩኒቨርሲቲዎች በሚተዳደረው በፍሌቸር የህግና የዲፕሎማሲ ትምህርት ቤት ከ1980-1982 .ም ድረስ በመማር ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በግንቦት 1982 .ምአግኝተዋል፡፡

ክቡር ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ከባለቤታቸው ክብርት ወ/ሮ መአዛ አብርሃ ጳውሎስ ሙላቱን አፍርተዋል፡፡ ዋና፣ እግርኳስ፣ ቴኒስና ረቂቅ ሙዚቃ በእረፍት ጊዜያቸው የሚያዘወትሯቸው መዝናኛዎቻቸው ናቸው፡፡

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

የኢፌዴሪ ፕሬዝደንት